የህብረቱ ጉባዔ ለከተማችን ድምቀትና የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሯል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለከተማችን ድምቀትና የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሯል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በደማቅ ሁኔታ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ማምሻውን ተጠናቅቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጉባዔውን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ÷”የህብረቱ ጉባዔ ለከተማችን ድምቀትና የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሯል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቱሪዝም መስህቦችን እና የከተማዋን መልካም ገጽታ እንዲሁም የነዋሪዎቿን ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
በጉባዔው አዲስ አበባ እንደወትሮው ሁሉ እንግዳ ተቀባይነትና ያለባትን ተደራራቢ ሃላፊነት ስራ ላቅ ያለ የማስተናገድ ብቃትን ያሳየችበት ነውም ነው ያሉት፡፡
“ተባብረን በጋራ በሰራነዉ ስራ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ወንድሞች እና እህቶቻችን ኩራት መሆናችንን ዳግም አሳይተናል “ሲሉም ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች የመዲናዋ ነዋሪዎች ላሳዩት ታላቅ እንግዳ አክባሪነትና ተቀባይነትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡