Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶቿን ወደ ሳዑዲ ላከች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር የሚወያይ ከፍተኛ የዲፕሎማቶች ልዑኳን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መላኳን አስታወቃለች፡፡

ልዑኩ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የክሬሚሊን ከፍተኛ አማካሪ በሆኑት ዩሪ ኡሽኮቭ የተመራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በነገው ዕለትም ከዋሽንግተን ልዑክ ጋር የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነት ወደ ሰላማዊ ድርድር ለማምጣት ያለመ ምክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይኪ ዋልትዝ እና በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቴቭ ዊትኮፍ ቀደም ብለው ሪያድ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡

በውይይቱ የዩክሬን ልዑክ እንደማይሳተፍ እና በግለሰብ ደረጃ ኬቭን ወክሎ የሚሳተፍ ዲፕሎማት ሊኖር እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም ያለመ የስልክ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ፑቲን ጉዳዩን በተመለከተ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ነገ የሚደረገው የሁለቱ ሀገራት ልዑካን ውይይት በስምምነት ፍፃሜውን የሚያገኝ ከሆነ፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው ሊወያዩ ይችላሉ መባሉን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.