Fana: At a Speed of Life!

ጉባዔው ትላልቅ ሁነቶችን በስኬት የማጠናቀቅ አቅማችን አሳይቷል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ በተቋማት ቅንጅት እና በህዝብ ባለቤትነት እየተመራን ትላልቅ ሁነቶችን በስኬት የማጠናቀቅ አቅማችን አሳይቷል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በስኬት መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዴዔታው፤ በጉባዔው ከወትሮው በተለየ መልኩ በርካታ እንግዶች እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የዘንድሮውን ጉባዔ ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያ በርካታ ዲፕሎማሲዊ ስኬቶችን ባከናወነችበት ወቅት መካሄዱ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡

ለጉባዔው ስኬት ከ35 በላይ ተቋማት የተውጠጡ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቅሮ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በሚገባ መወጣቱን አንስተው፤ ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በጉባዔው ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማሳካት ተችሏል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ የመጀመሪያው በተቋማት ቅንጅት እና በህዝብ ባለቤትነት እየተመራን ትላልቅ ሁነቶችን በስኬት የማጠናቀቅ አቅማችን ማሳየት የቻለ ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛው የሀገራችንን ስኬት እና አዲስ ገጽታ ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ መሆኑን ጠቁመው÷ የተገኙ አበይት ዲፕሎማሲያዊ ድሎችም የጉባዔው ስኬቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አጠቃላይ የተቋማትን ስምሪትና ቅንጅት የተሳለጠ በማድረግና በቅርበት በመከታተል የላቀ ድርሻ መወጣቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ሀገራችንን የሚመጥን አቀባበል እና ቆይታ እንዲኖራቸው ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.