Fana: At a Speed of Life!

የግሉ ዘርፍ ቱሪዝም ላይ እንዲሳተፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም እንዲሳተፍ መንግስት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን፥ ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንቅስቃሴ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለጎብኚዎች ተመራጭ ከሚያደርጓት አንዱና ዋነኛው የተለያዩ ባህሎች፣ መዳረሻዎች፣ ስፍራዎችና ጎብኚዎችን የሚስቡ መስህቦች መኖራቸው ነው ብለዋል፡፡

ማንኛውም ጎብኚ ኢትዮጵያ መጥቶ ባየው ነገር አለመደሰትና አለመዝናናት አይችልም ያሉት ሚኒስትሯ ፥ ኢትዮጵያ የተለያዩ መስህቦች መገኛ ብቻ ሳትሆን ምድረ-ቀደምት መሆኗ ተመራጭ ያደርጋታል ሲሉ አብራርተዋል።

ስለ ምድረ-ቀደምትነቷ ስናነሳ ስለዘመን አቆጣጠሯ፣ ስለፊደሏ፣ ቡናን ለዓለም ስለማስተዋወቋ፣ በቅኝ ስለአለመገዛቷና ከሌሎች በተለየ መልኩ ስለሚያስነሷት የሀገር ሃብቶቿ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ሥድስት ዓመታት ለቱሪዝም የተለየ ትኩረት እየተሰጠው እንደሆነ አንስተው፥ ቱሪዝም ከሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጮች መካከል አንዱ ተደርጎ በመንግስት ስለመወሰዱም ገልጸዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ቱሪዝም ከማሳደግ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝሙ እንዲሳተፍ ያደርጋል፤ ቱሪዝም በሀገር ግንባታ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል የማይባል እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ባሻገር በዓለም ተመራጭ የሆነ አየር መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለቱሪዝሙ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

እንደአብነትም አየር መንገዱን ተመራጭ በማድረግ ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቆይታ ለሚኖራቸው መንገደኞች በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን፣ ፓርኮችን እና መዝናኛ ስፍራዎችን ለመጎብኘት እድል ይሰጣል፡፡

የሚኒስቴሩን ዳታዎች በመጠቀም የቱሪዝም ሥፍራዎችና መስህቦች እንዲጎበኙ ለማስቻል ዘርፉ በተጠና መንገድ እንዲመራ እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል ሚኒስትሯ፡፡

ይህም ቱሪዝሙ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ የሚታይ ለውጥ እንዲያመጣ ያደርገዋል ሲሉ የጠቆሙት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለዘላቂ ልማት የቱሪዝም አቅምን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.