4ኛው ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ኮንፈረንስ በማራካሽ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አራተኛው ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በሞሮኮ ማራካሽ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
የሞሮኮ መንግሥት ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የከፍተኛ ደረጃ መድረኩ ዓለም አቀፍ መሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በዓለም ዙሪያ የመንገድ ደኅንነትን የማሳደግ ስልቶች ላይ ይወያያል።
በኮንፈረንሱ የአፍሪካ ህብረት የትራንስፖርትና ኢነርጂ ልዩ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዲሁም የመንገድ ደህንነትና ኢንሹራንስ ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ ተገኝተዋል።
ከየካቲት 11 እስከ 13 ቀን 2017 በሚቆየው የሶስት ቀናት የውይይት መድረክ በመንገድ ደህንነት ላይ ያሉ ቁልፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል።
እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እና የትራፊክ አደጋዎችን እና ጉዳቶችን ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖችን ያጠናክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡