የእሳት አደጋ መንስዔዎች …
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በየጊዜው የእሳት አደጋ በመኖሪያ እንዲሁም በንግድ ቤቶች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ተከስቶ ጉዳት ሲያደርስ ይስተዋላል፡፡
ታዲያ የእሳት አደጋ በምን ምክንያት ይከሰታል?
የእሳት አደጋ መንስዔዎችን በተመለከተ ሐሳባቸውን ያካፈሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ÷ የእሳት አደጋ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል የጥንቃቄ ጉድለት፣ ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ጋር መለማመድና የአየር ሁኔታ ዋነኞቹ ናቸው ይላሉ፡፡
አብዛኛው የእሳት አደጋ በጥንቃቄ ጉድለት እንደሚከሰት ጠቅሰው÷ ለአብነትም በኤሌክትሪክ ኃይል ከተገለገሉ በኋላ ሶኬት አለመንቀል፣ በሥራ ላይ መብራት ከጠፋ ሶኬት ሳይነቅሉ ከአካባቢው መራቅ፣ ለጋዝ ሲሊንደር ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግና ሲገለገሉ የቆዩትን የኤክትሪክ ምድጃ ሳያጠፉ መተኛት ይገኝበታል ብለዋል፡፡
ሌላው ለአደጋ አጋላጭ ምክንያት ቸልተኝነት ነው፤ ሁኔታው ችግር እንደሚያመጣ እያወቁ ግን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች ጋር መለማመድ ለእሳት አደጋ ያጋልጣል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የአየር ሁኔታ ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ በሚሆንበት ወቅት ለእሳት አደጋ መከሰትም ሆነ ከተከሰተ በኋላ በፍጥነት ለመዛመት መንስኤ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ከክረምት ይልቅ በበጋ የእሳት አደጋ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ወቅቱን ያማከለ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡
ፌደራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት የእሳት ቃጠሎ መንስዔዎችን በፎረንሲክ ምርመራ አጣርቶ ውጤቱን ይፋ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎ መንስዔዎቹም የኤሌክትሪክ ቴክኒካል ችግር እንዲሁም የመካኒካል ችግር፣ ሆን ተብሎ በሰው አማካኝነት የሚከሰቱ እና ቸልተኝነት መሆናቸውን ውጤቱ አመላክቷል ነው ያሉት፡፡
አደጋ ሲከሰት እንደ አደጋው ሁኔታ (ክብደት ወይም ቅለት) እና እንደ አቅምና ችሎታችን ቀለል ያለ ከሆነ ሳይዛመት በራስ አቅም ለማጥፋት መሞከር፤ የአካባቢው ሰዎችን አስተባብሮ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በፊት ዕቃዎችን ማውጣት የአደጋ መጠኑን እንደሚቀንስ አቶ ንጋቱ አብራርተዋል፡፡
አደጋው የከፋ ከሆነ ግን እራስን እና ቤተሰብን ከአደጋው መጠበቅና ማሸሽ አስፈላጊ ነው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ለኮሚሽኑ ሪፖርት ማድረግም ቸል ሊባል አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአጠቃላይ የጥንቃቄ መልዕክቶችን መተግበር፣ የአደጋ ቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት፣ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ገዝቶ ማስቀመጥ፣ ከተቀጣጣይ ነገሮች አካባቢ እሳት እንዳይኖር ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
በኤሌክትሪክ ከተገለገሉ በኋላ ኤሌክትሪክ ማቋረጥ (ሶኬቶችን መንቀል)፣ በሚገለገሉበት ወቅት መብራት ከጠፋ ሶኬት መንቀል፣ ለጋዝ ሲሊንደር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፣ የተገለገሉበትን የኤሌክትሪክ ምድጃ ማጥፋትና ለአደጋ የሚያጋልጡ ልምምዶችን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው