Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ልዑክ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንን ጎበኘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልዑካን ቡድን በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት ተገኝቶ ጉብኝት አድርጓል።

ልዑካኑ በተቋሙ ተዘዋውረው የተለያዩ የስራ ክፍሎችን ተመልክተዋል።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በፓርቲው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል የህዝብ መረጃ እና ኮሙኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር ዡ ሮንግሹይ ከተመራው ልዑክ ጋር በሚዲያ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።

በአሁኑ ወቅት የሚዲያ ተቋሙ በስምንት የሀገር ውስጥ እና በሁለት የውጭ ቋንቋዎች በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ እና በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች ከፍተኛ ቁጥር ላለው አድማጭ ተመልካች ተደራሽ መሆኑን አመልክተዋል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ባሻገር በመዝናኛው ዘርፍ ተመራጭ የሆኑ ይዘቶችን ወቅቱ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ፋና ብሪክስ ቲቪን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አቻ ሚዲያ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ በኢትዮጵያና በወዳጅ ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ እና የባህል ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑነ ተናግረዋል።

የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ጉብኝትም ተቋሙ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማሳደግ እያከናወነ ላለው ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ዡ ሮንግሹይ በበኩላቸው፥ በጉብኝታቸው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እየተጠቀመባቸው ያሉት ዘመናዊ መሳሪያዎች እና አሰራሮች ለጥራትና ለተደራሽነት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸው ገልጸዋል።

የህዝብ ለህዝብ እና የባህል ትስስርን ለማጠናከር ሚዲያ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው፥ መንግስታቸውም ሆነ ፓርቲያቸው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በስልጠና፣ በቴክኒክ ትብብር እና በልምድ ልውውጥ መስኮች ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በወንደሰን አረጋኽኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.