የምክክር ኮሚሽኑ የስራ ዘመን ተራዘመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሶስት ዓመታት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በመመርመር ለኮሚሽኑ የ1 ዓመት ተጨማሪ የስራ ዘመንን ሰጥቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች ኮሚቴ የኮሚሽኑን የስራ ሂደት ከገመገመ በኋላ ባደረገው ምልከታ ኮሚሸኑ አጠቃላይ ስራውን ማጠናቀቅ እንዲያስችለው የስራ ዘመኑ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር፡፡
ምክር ቤቱ ኮሚሽኑ ዋና ዋና እና አንኳር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን በማመን የስራ ዘመኑ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም በ3 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
አባላቱ ኮሚሽኑ በተሰጠው ተጨማሪ የስራ ዘመን ተጠባቂ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል።
የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማራዘም እንደሚቻል ይደነግጋል።
በመራኦል ከድር እና አሸናፊ ሽብሩ