የቬትናም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቬትናም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የሶሻሊስት ሪፐብሊክ ቬትናም የጋራ የፖለቲካ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በምክክሩ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ÷ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የቬትናም ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከቬትናም ፈጣን የኢንዱስትሪ እድገት ልምዶችን ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
የቬትናም ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ኑየን ሚን ሄን በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሀገራቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር በባለ ብዙ-ወገን መድረክ እና በደቡብ ደቡብ ትብብር ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ኢትዮጵያ እና ቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በቀጣይ ዓመት እንደሚያከብሩም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡