የኮሪደር ልማቱ ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲፈጠር አስችሏል- አለሙ ስሜ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው የኮሪደር ልማት ደህንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲፈጠር አስችሏል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
አራተኛው ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በሞሮኮ ማራካሽ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ(ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው የኮሪደር ልማት የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የትራፊክ አስተዳደር እና የተቀናጀ የህዝብ ትራንስፖርት እና የትራፊክ መጨናነቅ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን ማምጣቱን ገልፀዋል።
እንደ አፍሪካ የመንገድ ትራፊክ መንስኤዎች የአሽከርካሪዎች የባህሪ ችግር፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ጉድለት፣ በቂ የመንገድ መሠረተ ልማት ያለመኖር እና የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ስህተት መሆኑንም ጠቁመዋል።
አደጋውን ለመቀነስ የወጡ የመንገድ ትራፊክ ህጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ደህንነታቸው የተረጋገጡ የመንገድ መሠረተ ልማት ማስፋፋትና የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚሰሩ ስራዎች ላይ ህዝብን ተሳታፊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እንወስን፤ በጋራ እንቁም ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡