5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሎች ተጓጓዘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እስካሁን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሎች መጓጓዙን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት÷ በተያዘው ዓመት 24 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት እቅድ ተይዞ ነበር ።
በዚህም እስካሁን 7 ሚሊየን ኩንታል የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን እና 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታሉ ደግሞ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች መጓጓዙን ገልጸዋል ።
ከዚህ ቀደም በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት ከሀረሪ ክልል እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ውጭ ሁሉም ክልሎች በአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ እንዲካተቱ እና አልሚ ባለሃብቶች ደግሞ በሚያለሙበት ክልል ማዳበሪያ እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት ።
በተጨማሪም በአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት በዚህ ዓመት የዲጂታል አሰራር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል ።
በመሳፍንት እያዩ