አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ልዑክ ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቫለንቲና ማትቪዬንኮ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ፡፡
በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የረጅም ጊዜ የታሪክና የባሕል ግንኙነት እንዳላቸው ያነሱት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ፤ ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂክ ግንኙነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትናንት ምሽት አዲስ አበባ የገባው ልዑኩ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ቀደም ሲል ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ መፈራረማቸውም ይታወሳል፡፡
አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ለፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ እድገት ላበረከቱት የጎላ አስተዋጽኦ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የክብር ኒሻን ተሸልመዋል፡፡
ሽልማቱ ለፌዴሬሽን ፓርላሜንታዊ እድገት የበለጠ እንዲሠሩ የሚያበረታታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የክብር ኒሻኑ ለምክር ቤቶች ፓርላሜንታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለሩሲያና ለውጭ ሀገራት ዜጎች የሚሰጥ መሆኑን የሩሲያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሚስዝ ቫለቲና ማትቬንኮ ገልጸዋል፡፡
በሰለሞን በየነ