አሥተዳደሩ ከ111 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሥድስት ወራት ከ111 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
የአሥተዳደሩ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ የግማሽ ዓመቱን አፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ 125 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 111 ነጥብ 5 ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ37 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
የገቢና ወጪ መጣጣም ብሎም እድገቱ ከተማዋ ምን ያህል በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንደሆነች ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያነሱትን የመሰረተ ልማት ጥያቄ የመፍታት ስራ ሲሰራ መቆየቱን በመግለጽ የመብራት፣ የውሃና የመንገድ ችግር የነበረባቸው ኢንዱስትሪዎችን በመለየት የ231 ኢንዱስትሪዎች ችግር እንዲፈታ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከ8 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ወደ ቫት ስርዓት እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰው÷ ለ1 ሺህ 8 ባለሃብቶች የኢንቨትስትመንት ፍቃድ እድሳት መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
የተማሪ ቅበላን 1 ሚሊየን 253 ሺህ 737 ማድረስ ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ÷ 835 ሺህ 69 ተማሪዎችም የምገባ አገልግሎት እያኙ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በየሻምበል ምኅረት