ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የመከላከያ ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የመከላከያ ልዑካን ቡድን በዓለም አቀፍ የመከላከያ አውደ ርዕይ እና ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
አውደ ርዕዩ እና ኮንፈረንሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት 21 ቀን 2025 የሚካሄድ ሲሆን÷ ለወታደራዊ ኢንዱስትሪ እድገት ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ልምዶች የሚወሰዱበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዚሁ ወቅት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መከላከያ ኤታማዦር ሹም ኢሳ ሰይፍ መሀመድ አል ማዝሮኢ እና ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተገናኝተው በሁለቱ እህትማማች ተቋማት ሁለትዮሽ ትብብር አስመልክቶ መወያየታቸውን በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡
የሁለትዮሽ ውይይቱ ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም ባሻገር የተቋማቱንና የወደፊት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑም ተገልጿል፡፡