በመዲናዋ ለዕይታ ግልጽ ያልሆነ ሰሌዳ በለጠፉ ተሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ ሊወሰድ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የታጠፈ፣ የደበዘዘ እና የተፋፋቀ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በከተማው ለእይታ ግልጽ ያልሆኑ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች መበራከት ለአደጋ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውን ፖሊስ ገልጿል፡፡
በየጊዜው የታጠፈ፣ የደበዘዘና የተፋፋቀ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ሕጋዊ ርምጃ እየተወሰደ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
በዚህም ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓትን በመፍጠር ሕጋዊ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ታምኖበታል።
በቅርቡ ተግባራዊ በሆነው ደምብ ቁጥር 557/2016 መሰረት ለዕይታ ግልጽ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 1ሺህ 500 ብር የሚያስቀጣ ደምብ መተላለፍ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በዚህም ከየካቲት16 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የታጠፈ፣ የተቆረጠ፣ የደበዘዘ እና በአጠቃላይ ለዕይታ ግልጽ ያልሆነ ሰሌዳ ለጥፈው በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡