እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ እድገት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በቅርቡ የተጀመረውን የካፒታል ገበያ ለማሳደግ እንግሊዝ ድጋፍ እንደምታደርግ የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ የኢኮኖሚ የትብብር ዘርፎች ላይ አተኩረው በሰጡት መግለጫ÷በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ልማት ትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ የእንግሊዝ ባለሃብቶች በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት እና ሌሎች ዘርፍች ላይ ኢንቨስትመንታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በይፋ የጀመረችውን የካፒታል ገበያ በይበልጥ ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጀመረችውን ጉዞ ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ፥ በዘርፉ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው ፥ መንግስት የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ኢኮኖሚውን እንዳነቃቁት ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም ባለፉት ሥድስት ዓመታት በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት ትላልቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች የበለጠ ትርፋማ በመሆን በኢኮኖሚው ላይ የተሻለ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በፈጣን የዕድገት ጉዞ ላይ ናት ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ፥ የእንግሊዝ መንግስት በተለያዩ የልማት ስራዎች እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ እንደገለጹት ፥ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ በወሰዳቸው ርምጃዎች የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ጨምሮ ቁልፍ ተቋማት እንዲቋቋሙ አድርጓል።
በዚህም የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው ፥ የእንግሊዝ መንግስት ገበያው ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ላደረገው የቴክኒክ እና መሰል ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል።