በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት መስራት ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የተጀመሩ የጋራ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ።
የጋምቤላ እና የኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማበር ኮር በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የቆየ የአብሮነት እሴት ይበልጥ በማጠናከር ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የክልሎቹ ወንድማማች ህዝቦች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በጋራ በመሻገር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በጋራ እየሰሩ የኖሩ ናቸው ብለዋል።
የጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሮምሳ ሰለሞን በበኩላቸው ፥በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለውን የአብሮነት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በሁለቱ ክልሎች ተጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች የተጀመሩ የጋራ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ መግለጻቸውን የጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።