የኢትዮ-ሩሲያ ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል-ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው ዘመን ተሻጋሪ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ ከሩሲያ ፌዴሬሽን የፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቫለንቲና ማትቪንኮ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም፥ የኢትዮጵያና ሩሲያን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ ፕሬዚዳንት ታዬ፥ ሁለቱ ሀገራት በሳይንስ፣ ትምህርት፣ ባህል እንዲሁም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስኮች ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
አፈ-ጉባዔ ቫለንቲና ማትቪንኮ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሀገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከፕሬዚዳንቱ ጋርም በተለያዩ የትብብር መስኮች ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኢኮኖሚው መስክ ጠንካራ ግንኙነት ለመገንባት ቁርጠኛ እንደሆኑ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡