Fana: At a Speed of Life!

150 ሺህ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በበይነ መረብ ለመፈተን ዝግጅት እየተደረገ ነው

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 150 ሺህ የሚደርሱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናቸውን በበይነ መረብ እንዲወስዱ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በአጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ እንዳሉት÷ በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን የተናበበ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

በተለይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘት ረገድ እኩል እድል እንዲኖረው፤በድሃና ሃብታም መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠብ ሥራ መስራት አለብን ነው ያሉት።

ሀገሪቱን መለወጥ የሚቻለው የትምህርት ሥርዓቱን መቀየር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው÷በርካታ ሪፎርሞች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በመንግስት ት/ቤቶች የተሻለ የመማር ማስተማር እንዲኖር ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል የተጀመረው ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከፈተና ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት 150 ሺህ የሚደርሱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናቸውን በበይነ መረብ እንዲወስዱ ቅድመ ዝግጅ እየተደረገ አንደሆነ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የ2ኛ ደረጃ የመማሪያ መጽሐፍትን አንድ ለአንድ ማዳረስ መቻሉን ገልፀው÷የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተማሪ መጽሐፍ አንድ ለአንድ ያልደረሰ በመሆኑ ክልሎች በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመምህራንን አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከተመረቁ ዜጎች ውስጥ ልዩ የማስተማር ሙያ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ወደ ሙያው እንዲገቡ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.