Fana: At a Speed of Life!

ኔዘርላንድስ ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነቷን እንደምታጠናክር አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብቶች መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ማርክ ዘለንራት ጋር መክረዋል።

ውይይቱ ለጋራ ጥቅም በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትብብር ማሳደግን አስመልክቶ ነውም ተብሏል።

በኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ፥ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥና በቀጣናው መልካም አስተዳደርን፣ ተጠያቂነትን እንዲሁም ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ለዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

መንግስት አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አፅንዖት በመስጠት፥ በሁለቱ ሀገራት መካከል በፍልሰት፣ በጸጥታና በልማት ዘርፍ ቀጣይነት ያለው ትብብር እንዳለም ጠቁመዋል አምባሳደሩ።

ማርክ ዘለንራት በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው፣ የሀገራቱ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የበለጠ እንደሚጠናከር ማረጋገጣቸውን በብራስልስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ከሆኑት ከጄልቴ ቫን ዋይረን ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ፣ የዓለም ፖለቲካ፣ የጸጥታ እና የሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ጄልቴ ቫን ዋይረን በዚህ ወቅት ፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ በኩል ያላትን ሚና ገልጸው ፥ በቅርቡ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.