ኢትዮጵያ በቀጣናው እየተወጣች ያለው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ይደነቃል- የተባበሩት መንግሥታት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናው እየተወጣች ያለውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ እና የጸጥታና ደኅንነት ኃላፊ ጊልስ ሚቻውድ አደነቁ፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ከጊልስ ሚቻውድ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ቁልፍ አጋር መሆኗን ምክትል ዋና ፀሐፊው አንስተዋል፡፡
መንግሥታቱ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚያደርገው ወሳኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የልማት እና የሰላም ግንባታ ጥረት የኢትዮጵያን አስተዋጽኦ አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርና ለተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ለምትሠራቸው ሥራዎችም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ እና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ አካላት የምታደርገውን ድጋፍ ቀጣይነት በማረጋገጥ፤ አጋርነቷን ትቀጥላላች ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ከጊልስ ሚቻውድ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የባለብዙ ወገን ማዕከል መሆኗን ያስረዱት ሚኒስትር ዴዔታው፤ ይህም በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥታቱ ሠራተኞችን ደኅንነት የማረጋገጥ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለው አንስተዋል፡፡
ጊልስ ሚቻውድ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ የምታደርገውን ጉልህ አስተዋጽኦ አድንቀው፤ ሀገሪቱ ለተባበሩት መንግሥታት ሥራዎች የምትሰጠው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡