ታጂኪስታን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር አደነቀች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከታጂኪስታን የኢኮኖሚ ልማትና ንግድ ሚኒስትር ዛቭኪዞዳ ዛቭኪ አሚን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አምባሳደር ጀማል÷ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ያደረገችውን ስኬታማ ሽግግር አስመልክተው ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ በርካታ ተነሳሽነቶች መጀመሯንም አብራርተዋል፡፡
በዚህም በግብርና፣ በውሃ እና በሃይል ዘርፎች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል ብሔራዊ የማስተካከያ ዕቅድ መጀመሩን አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደተተከሉ መናገራቸውንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2030 የካርበን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ የሚያስችል ለአየር ንብረት ለውጥ ተቋቋሚ የሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዛቭኪዞዳ ዛቭኪ አሚን በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ያደረገችውን ስኬታማ ሽግግር አድንቀዋል፡፡
በኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ሃይልና በሌሎች ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማሳደግ መንግስታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡