የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጎንደር ከተማ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችንና የኢንቨስትመንት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የፌዴራል ከፍተኛ አመራር አባላት ከጎበኙት መካከል በክልሉ መንግስትና ባለሀብቶች በጋራ የተቋቋመው የአባይ ጋርመንት የአልባሳት ማምረቻ ይገኝበታል።
በተጨማሪም በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው የፒያሳና አካባቢው የኮሪደር ልማት ስራ እና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት የቅርስ ጥገናና እድሳት ስራም የጉብኝቱ አካል መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው ።
ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎቹ በከተማው በሚካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ እንደሚሳተፉም ተጠቁሟል።
በተመሳሳይ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በአርባ ምንጭ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚህ ጉብኝት ላይ የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሺዴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት በባሕርዳር ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በጂግጂጋ ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።