የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ማሳካት ይገባል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እና ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት በርብርብ መስራት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት በሸገር ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሕዝብ ኮንፈረንስ ላይ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ፥ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎችም ዘርፎች ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ወደ ከፍታ የሚወስዱና የህዝቡን መሻት የሚያረጋግጡ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት።
ፓርቲው በ2ኛ መደበኛ ጉባዔው የኢትዮጵያንና የህዝቧን ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሁም ሀገሪቱ በዓለም ተገቢውን ስፍራ እንድትይዝ የሚያደርጉ ውሳኔዎች ማስተላለፉን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመተግበር ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካትና የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በርብርብ ማፋጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ፓርቲው ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ገዥ ትርክት እንዲፈጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን በማዳበር ዘላቂ የሰላም ግንባታን ለማፋጠን አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፥ ለስኬቱ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለሰላማዊ ውይይት ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የፓርቲው ምክር ቤት አባልና የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አሰፋ ÷ብልፅግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰው ፣ በተለይ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና እንድታደርግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በመደመር እሳቤ የተመዘገቡ ድሎችን በማስቀጠል የሀገር ግንባታ ግባችንን እናሳካለን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።