Fana: At a Speed of Life!

ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የመገንባቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ብልፅግናን የማረጋገጥና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የመገንባቱ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

“ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው ባሳለፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የሕዝብ ኮንፈረንስ በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።

በኮንፍረንሱ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እንደተናገሩት ፥ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ግብ የበለፀገችና ሕብረ-ብሔራዊነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።

በዚህም በቀጣይ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የመገንባቱ ተግባር ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በየዘርፉ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በሁሉም የልማት መስኮች ሕዝቡ በአቅሙና በችሎታው እንዲሰማራ እድል በመፍጠር ተሳታፊነቱንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በተለይም ለወጣቶች በቴክኖሎጂ በታገዘ የስራ እድል በመፍጠር ዘላቂ ሰላምንና ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው ያሳላፋቸውን ውሳኔዎች እስከታች ድረስ በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም መላው ሕዝብ እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፥ የጋራ ጠላታችን በሆነው ድህነት ላይ በመዝመት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሰላም ማስፈን ላይ በትኩረት መስራት አለብን ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ባህር ዳር ከተማን ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ትናንት ምሽት የተመለከቱት የኮሪደር ልማት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የባህር ዳር ከተማን ሰላም በማፅናት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.