ኢትዮጵያና እንግሊዝ ያላቸውን የቆየ ጠንካራ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተካሄደው የቡድን-20 ሃገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን ከእንግሊዙ አቻቸው ዴቪድ ላሚ ጋር መክረዋል።
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች ለሀገራቱ የጋራ ጥቅም በሚሰሩ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ፍሬያማ የትብብር ግንኙነት ወደላቀ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የእንግሊዝ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማሩበት ሰፊ እድል ስለመኖሩም አጽንኦት መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማነቃቃትና የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፋፋትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቅርበት ለመስራት ተስማምተዋል።