ኢትዮጵያና ታጂኪስታን በአቪዬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከታጂኪስታን የሲቪል አቪዬሽን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ናዛርዞዳ ሀቢቡሎ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበቸውና በተለይ በአቪዬሽኑ ዘርፍ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በተጨማሪም የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ቱሪዝምን ለማሳደግ በሚረዱ የትብብር መንገዶች እና በታላቁ የኢትዮዽያ አየር መንገድ በኩል የአየር ትስስር መፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ጀማል÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ እንዲሁም ፈጣን የአውታረ መረብ መስፋፋት በአቪዬሽን ዘርፍ በዓለም ግንባር ቀደም ከሆኑት አየር መንገዶች መካከል አንዱ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በታጂኪስታን እና በኢትዮጵያ መካከል ቀጥተኛ የጭነት በረራዎችን በመጀመርያ ደረጃ መጀመር አስፈላጊ ስለመሆኑም ለዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ከታጂኪስታን የሲቪል አቪዬሽን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ናዛርዞዳ ሀቢቡሎ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያስመዘገበችውን እድገት አድንቀዋል፡፡
መንግሥታቸው በአቪዬሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ ስለመሆኑ በመግለጽ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግ ማረጋገጣቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።