ቻይና ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት ድጋፏን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና ለኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለጀመረችው ሂደት ድጋፏን እንደምታደርግ አስታውቃለች።
የንግድ ድርጅቱን በመቀላቀል ሂደት ውስጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው÷በዓለም የንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ አምባሳደር ቼንግጋንግ ሊ ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ፀጋአብ፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና የረጅም ጊዜ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸው ቻይና በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እና በተለያዩ መስኮች ያላት ወሳኝ ሚና አንስተዋል።
ለልዑኩ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የጀመረችውን ሂደት ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ድርጅቱን የመቀላቀል እቅዱ እውን እንዲሆን ቻይናን ጨምሮ ቁልፍ ከሆኑ የንግድ አጋር አገራት የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮች ወሳኝ እንደሆኑም መግለጻቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በዓለም የንግድ ድርጅት የቻይና ልዑክ አምባሳደር ቼንግጋንግ ሊ በበኩላቸው÷ ቻይና ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው ሂደት ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡