ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች ነው-ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አባይ ወንዝን በማልማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለፁ፡፡
19ኛው የናይል ቀን “የናይል ትብብርን ማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ የተፋሰሱ አባል ሃገራት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት÷ ናይል ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር የአንድነትና የተስፋ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ለልማት ትብብር የቅድሚያ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ አባይ ወንዝን በማልማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር (ኢ/ር) ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው÷ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ምን መደረግ እንዳለበት በተፋሰሱ የሚኒስትሮች ጉባኤ መምከራቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመግንባት ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ÷ የናይል ተፋሰስ ትብብር አባል ሀገራቱ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰባቸው ያለውን ተፅእኖ ለመቋቋም በድንበር ዘለል ውሃ ሀብቶች የጋራ ልማትና አጠቃቀም ማዕቀፍ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡
በጎህ ንጉሱ እና ነፃነት ፀጋይ