መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው – ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወልቂጤ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሔደ ይገኛል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፥ እንደ ሀገር በርካታ ፈተናዎችን እየተሻገርን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ከአመራሩ ባለፈ ከመላው ህዝብ ጋር የጋራ ተግባቦት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ፓርቲውን ማጠናከር እና ጥራት ባለው ሃሳብ የሚመራበትን ምህዳር መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በመጀመሪያው የፓርቲ ጉባኤ ላይ ተረጂነትን መጸየፍ የሚችል ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የጋራ ተግባቦት መፍጠር መቻሉን ገልጸው፥ ባሉን ጸጋዎች ላይ በማተኮር በልማት ስራ ላይ ማተኮር ተችሏል ብለዋል።
ይህን ተከትሎም ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከማስቀረት ባለፈ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ውጤታማ እንደነበር ገልጸው፥ በዲፕሎማሲው መስክ የሀገርን ክብር ማስጠበቅ የሚያስችል ስራ ተግባራዊ ማድረግ ስለመቻሉም በአብነት ጠቅሰዋል።
ሰጥቶ በመቀበል በህገ መንግስታዊ ስርዓት እና የዓለም አቀፍ መርህን በተከተለ መልኩ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራችንን አስቀጥለናልም ብለዋል ሚኒስትሯ።
በጠንካራ ፓርቲ እና መንግስት እንዲሁም በህዝባችን ተሳትፎ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አላጋጠመንም ሲሉም ገልጸዋል።
ብሔራዊ ገዢ ትርክት ለሀገሪቱ ህዝቦች ከሚኖረው የላቀ ጠቀሜታ አንጻር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የላቀ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ውጤታማ የሰላም እና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራን በተሻለ ደረጃ በመፈጸም ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ አመልክተው፤ ያልተቋረጠ የኢኮኖሚያዊ ግንባታ ስራ ቀጣይነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዘላቂ የስራ እድል መፍጠር እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አመላክተዋል።
የመስኖ ተጠቃሚነትን ማጎልበት፣ አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ ተገቢ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ የሚገኘውን ሃብት ማጎልበት ይገባል ሲሉም ሚኒስትሯ ማብራራታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።