በሆሳዕና ከተማ የህዝብ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የህዝብ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
መድረኩን የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ፍቃዱ ተሰማ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እየመሩት ይገኛል።
የውይይት መድረኩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በተገኙበት ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በውይይቱ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አንዮ÷ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራው የሰላም ጉዳይ ላይ ነው ያሉ ሲሆን በዚህም በዞኑ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንደሌለ አስታውቀዋል።
በዞኑ ምርታማነትን ለመጨመር ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በተገቢው መጠንና ሰዓት በማቅረብ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚሰራው ስራ አመርቂ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ ገልጸው፤ ህገወጥ የህጻናት ዝውውርን ለመከላከልም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ከማህበረሰቡ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘመን በየነ