ፆምና የጤና ጠቀሜታው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚፆመው የዐቢይ ፆም የተጀመረ ሲሆን የእስልምና እምነት ተከታዮችም ከቀናት በኋላ የረመዳን ፆምን ይጀምራሉ፡፡
በሁለቱም እምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ከሚሰጣቸው የጾም ወቅቶች ጋር ተያይዞም የፆም ጠቀሜታዎች ለማንሳት ወደናል።
ፆም በበርካታ ህዝቦች የሚከወን እና በተለይም በሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር ነው።
ከዚህ ቀደም የወጡ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት በቀን ከ16 እስከ 18 ሰዓት ምግብ ሳይመገቡ ማሳለፍ የተለያዩ የጤና በረከቶችን ያስገኛል።
በመሆኑ ከፆም የሚገኙ የጤና ጠቀሜታዎች ምንድ ናቸው?
በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር፣ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጾም በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በተሻለ መንገድ ለመቆጣጠርና በተለይም የስኳር በሽታ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ጠቃሚ መሆኑ ነው የተጠቆመው።
እብጠትን በመከላከል ሰዎች ጤናማ እንዲሆኑ ያስችላል ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጡ ጥናቶች በጾም ወቅት ሰውነት የሚያገኘው የካሎሪ መጠን ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ ሰውነት ላይ የሚከሰት እብጠት እንደሚቀንስ ያሳያሉ።
የደም ግፊትን እና የኮሌስትሮል መጠንን ለመከላከል ለከፍተኛ ክብደት የተጋለጡ ሰዎች በተደጋጋሚ እንዲፆሙ ተደርጎ የሰውነት ክብደታቸው መቀነሱ ተጠቅሷል።
የሰውነት ክብደታቸው መቀነሱ ደግሞ የደም ግፊታቸውና የኮሌስትሮል መጠናቸው እንዲቀንስ ረድቷቸዋል፤ ይህ ደግሞ ከልክ በላይ በሆነ ውፍረት ሊከሰት የሚችለውን የልብ ጤንነት ችግር መቅረፍ ያስችላልም ነው የተባለው።
ፆም የአዕምሮ የመስራት አቅምን ያፋጥናል፣ ከነርቭ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ይከላከላል፣ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፣ ካንሰርን ለመከላከል እና ለምግብ መፈጨትና የስርዓተ ምግብ መንሸራሸርን ለማፋጠን ይረዳል።
እንዲሁም ክብደት ለመቀነስ እና አጥንትን ለማጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሆርሞን እድገት ለመጨመር እንደሚረዳም ነው የተጠቆመው።
ምንጭ፦ healthline.com