Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቻይና የኢንቨስትመንት ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ- ቻይና የ2025 የኢኮኖሚ እና ንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት የተመቸ እምቅ አቅም አላት፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢንዱስትሪ መስፋፋትና ልማትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸው÷በለውጡ አካታችና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር በፈጣን እድገት ላይ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ የቻይና ባለሃብቶች እድሉን አጠናክረው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊና ባህላዊ ሃብቶች የታደለች ሀገር መሆኗን አውስተው÷በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው ሁሉን አቀፍ ትብብር ትልቅ እድገት እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና የላቀ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋሮች መሆናቸውን የገለፁት አምባሳደሩ÷ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ተጨማሪ የትብብር አቅምን ያሳድጋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.