በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 7 የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ስራ ይጀምራሉ ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀጣይ ሁለት ወራት ሰባት የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንደሚጀምሩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዑስማን ሱሩር ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት ብሔራዊ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በክልሉ እየተተገበረ ይገኛል።
በመርሐ-ግብሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑን የገለጹት አቶ ዑስማን ሱሩር፤ የወተት ምርትና ምርታማነትን መጨመር ላይ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ የአምራቾች ቁጥር መጨመሩንና የወተት ምርትም ማደጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ሰባት አዳዲስ የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
ይህም የወተት ምርትን ለማሳደግና ለስራ ዕድል ፈጠራ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፥ የዶሮ፣ እንቁላል፣ ንብ ማነብ እና የዓሣ ልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል።
ይህም እንደ ሀገር የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል እና ስርዓተ ምግብን የማሻሻል ጉዞ እውን በማድረግ ረገድ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እንዳሉ የሚያሳይ ነው ሲሉ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።