የማህበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ በሽታን መከላከል ይገባል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከጌትስ ፋውንዴሽን የጤና ቡድኖች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስቴር ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡት ዶክተር መቅደስ፥ በአጋሮች የሚተገበሩ ፕሮግራሞች ከጤና ሚኒስቴር እና ብሔራዊ ስትራቴጂዎች ጋር የተናበቡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የእናቶችና ህጻናት ጤና እና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አገልግሎትን ማሳደግ ጤና ሚኒስቴር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም የማህበረሰብ ተሳትፎን በማሳደግ በሽታን መከላከል ይገባል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የጤና ፋይናንስ፣ የቤተሰብ እቅድ፣ ተዋልዶ ጤና፣ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።