ከዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቡ ጋር በትብብር ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል- ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር በፓርቲው አመራር ሰጪነት በየመስኩ የተገኙ ውጤቶች እና በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲሁም ውሳኔዎች ላይ ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ፓርቲው በሁለተኛው መደበኛ ጉባዔው የኢትዮጵያን ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል ብለዋል።
ውሳኔና አቅጣጫዎቹ በአግባቡ የሚተገበሩት ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው መሆኑን ገልጸው፤ በዛሬው ዕለትም በውሳኔና አቅጣጫዎቹ ዙሪያ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይት የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፓርቲው በሁሉም መስክ ያስመዘገባቸውን ድሎች ለማስቀጠል ትብብሮች ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር በተለያዩ መስኮች የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑንም አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል በበኩላቸው የፓርቲው ሀሳቦች ከኢትዮጵያ አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ተግባራዊ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ዛሬ የተደረገው ውይይትም ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎቹ መካከል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ለላቀ ውጤት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።