ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ለማጠናከር የ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ለማጠናከር የ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) በኩል በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች ለአራት አመታት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ፣ በኢትዮጵያ የጃይካ ኃላፊ ኬንሱኬ ኦሺማና የፋኦ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የግብርና ስርዓትን ለማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅምን ለማሳደግ ይውላል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
ፕሮጀክቱ የተራቆቱ የእርሻ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የሰብል ምርትን ለማሻሻል የሚረዱና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
ጥራት ያለው ምርጥ ዘር አቅርቦትን ማሻሻል፣ የምርት ብክነትን መቀነስና የገበያ እድሎችን መጨመር ላይ ፕሮጀክቱ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል።