Fana: At a Speed of Life!

በአፋርና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ሲከሰት የነበረውን ግጭት ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶች ውጤት እያመጡ እንደሆነ ግጭቱን ለማስቆም የተቋቋመው የፌደራል እና የክልል መንግስታት አብይ ኮሚቴ ስብሰባውን ባደረገበት ጊዜ ተገልጿል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የፌደራል እና የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ያቀፈው አብይ ኮሚቴ ዛሬ ስብሰባውን ያደረገ ሲሆን፤ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ወራት ተኩስ እንዲቆም በማድረግ፣ በየደረጃው የሰላም ውይይቶችን በማድረግ፣ የተፈናቃዮችን መረጃ በማጥራት የተሰራው ስራ አመርቂ እና ለቀጣይ ስራዎችን መደላድል የሚፈጥሩ መሆኑ ተናግረዋል።
ለመጣው ውጤት የሁለቱን ክልል አመራሮች እና የቴክኒከ ኮሚቴውን አመስግነዋል።
እስካሁን ግጭትን ለማስቆም እና ዘላቂ ሰላምን ለማረገገጥ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ በተሰሩ ስራዎች በአካባቢዎቹ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፈን የተሰራዉን ስራ በማጠናከር ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው የተከሰተው ግጭት ሁለቱ ማህበረሰቦች ለብዙ ዘመናት አብረው ከመኖራቸው፣ ካላቸው ማህበራዊ መቀራረብ እና የዳበረ የሰላም እሴት አንጻር መከሰት ያልነበረበት እንደሆነ አውስተዋል።
አክለውም አሁን የተፈጠረው መቀራረብ እንደ እድል በመውሰድ ሁሉም በባለቤትነት ስሜት የሚሰራ እና ሌላውን ማህበረሰብ እንደራሱ በማየት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚተጋ ከሆነ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እስካሁን በቅንጅት በተሰሩ ስራዎች የተገጙ ውጤቶች መልካም መሆናቸውን አንስተው፤ አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮችን በተለይም የተፈጠረውን ሰላም የማስፈን ስራ ህዝቡ በባለቤትነት እንዲይዘው በማድረግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የጋራ ስራዎችን በፍጥነት መተግበር ላይ ያለ ውስንነት እና አልፎ አልፎ የሚታዩ አንዳንድ ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮች በማረም ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራዎቻችንን መከወን ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም በአጠረ ጊዜ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲኖሩ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ በትኩረት እና በትጋት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ የታዩ ክፍተቶችን በመሻገር በሁለቱም ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ ባለው ቅዱሱ የረመዳን ወር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ እና እርቀ ሰላምን የሚፈጥሩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.