ሚኒስቴሩ ከአውሮፓ ህብረት የሴቶች ጉዳይ ጋር የጋራ ትብብሮችን ለማጠናከር ተስማማ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ከሆኑት ሶፊ ፍሮመስበርገር ጋር በሚኒስቴሩ ዋና ዋና ስራዎች ላይ የጋራ ትብብሮችን ለማጠናከር ያለመ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለህጻናት እንዲሁም ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን የማህበራዊ ጥበቃ ድጋፎች አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትሯ የተቋሙ የትኩረት አቅጣጫዎች የሆኑትን “ሴቶች በግብርና” ፕሮግራም፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የወጣቶች ስብእና ግንባታ ተቋማት ስራዎችን ዝርዝር ስኬቶች አንስተዋል።
የህብረቱ አምባሳደር ሶፊ ፍሮመስበርገር በበኩላቸው፤ በሚኒስቴሩ የሚሰሩ ስራዎችን ስፋት ያደነቁ ሲሆን በተጨማሪም ህብረቱ ድጋፍ ከሚሰጥባቸው የማህበራዊ ጥበቃ ዋና ዋና ፕሮግራሞች በተጨማሪ በተፈቃናዮች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ዙሪያ ህብረቱ ድጋፉን ይቀጥላል ብለዋል።
አምባሳደሯ አክለውም በተለያዩ ዘርፎች የሴቶችን አቅም የሚያሳድጉ ፕሮግራሞችን የአውሮፓ ህብረት እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት የሴቶች ጉዳዮችን የሚመለከታቸው ተቋማትን ማለትም ሚኒስቴሩን ጨምሮ ተያያዥ ተቋማትን የማጠናከር ፕሮግራም ወደ ስራ ለማስገባት ሂደት ላይ መሆኑ ከህብረቱ ጋር ያለ ጠንካራ አጋርነት ውጤት እንደሆነ መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።