Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ ውስንነቶቹን በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ እንደሚሰራ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገለጸ፡፡

የኃይል አቅርቦት አስተማማኝነት፣ ጥራት እና የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል አዳዲስ ዕቅዶች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።

ዕቅዶቹን በተመለከተ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በዚህ ወቅት÷ አገልግሎቱ ያሉበትን በርካታ ውስንነቶች በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ከፍ ለማድረግ ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኃይል አቅርቦት ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ÷ በለውጡ ዓመታት በሌሎች ድርጅቶች ላይ የታዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲደገም እየተሰራ ነው።

ደንበኞች በተቋሙ ብልሹ አሰራሮችን ሲመለከቱ ጥቆማ የሚሰጡበት የስልክ መተግበሪያ፣ የበይነ መረብ ገፅ እና የቴሌግራም መልዕክት መላኪያ ቦት ይፋ ተደርጓል።

ዜጎች የአሰራርና አስተዳደር ችግሮችን በማጋለጥ እንዲሁም መሰረተ-ልማቱን በመጠበቅ ተባባሪ እንዲሆኑም ተጠይቋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.