ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በእሳት አደጋ የደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በእሳት አደጋ የደረሰውን ጉዳት ተመልክተዋል፡፡
ዛሬ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ከ35 ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ወረዳ 6 ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ በመኖሪያና ንግድ ቤቶች ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
ከንቲባዋ በእሳት አደጋው የደረሰውን ጉዳት በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡
በአካባቢው ያሉ ቤቶች የተገነቡበት ግብአት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው አደጋው እንዲሰፋ ማድረጋቸውን የከተማዋ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሃመድ ተናግረዋል፡፡
አደጋውን ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ሰራተኞች በፍጥነት ደርሰው ሰፊ ርብርብ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ሆኖም አካባቢው መኪና የማያስገባ በመሆኑና ተቀጣጣይ ነገሮች በመኖራቸው የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል::