የዓድዋ የድል በዓልን የምናከብረዉ የድሉን ትሩፋቶች በልማትና በሰላም ዘርፍ ለመድገም ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ የድል በዓልን የምናከብረዉ የድሉን ትሩፋቶች በልማትና በሰላም ዘርፍ ለመድገም ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
“ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል’’ በሚል መሪ ሀሳብ 129ኛዉ የዓድዋ የድል በዓል በመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ደረጃ ሲከበር ዓድዋ ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ካበረከተቻቸዉ ድሎች ውስጥ ወርቃማው ታሪክ መሆኑ ተገልጿል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዓድዋ የድል በዓልን የምናከብረዉ የኢትዮጵያ ጀግኖችን ከመዘከር ባሻገር የጥቁር ህዝቦች ኩራት በመሆኑ እና የዓድዋ ትሩፋቶችን በሀገራችን በልማትና በሰላም ዘርፍ ለመድገም ነው ብለዋል።
በሕብረትና አንድነት እንዲሁም በተባበረ ክንድ የተገኘውን የዓድዋ ድል በዓል በልዩ ድምቀት ማክበርና ለትዉልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ድሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና ትብብር በላቀ ደረጃ የጸናበትና የአመራር ጥበብ ጎልቶ የታየበት መሆኑ ጠቅሰው፤ የአሁኑ ትዉልድ በጋራ መቆምን፣ ህብረትን፣ ጥንካሬን፣ የልማትና ዴሞክራሲ ጽናትን ከድሉ መማር እንዳለበት አመልክተዋል።
ለሀገር ሉዓላዊነትና ክብር መዋደቅ የዓድዋ ድል ትሩፋት መሆኑን ገልጸው፤ ህዝባችን ዛሬና ነገም በጋራ ሉዋላዊነትን ለማረጋገጥ እና ከተረጂነት ለመውጣት በልማቱና በሰላሙ ዘርፍ መረባረብ አለበት ብለዋል።
በተለይም በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገዉ ጥረት ዜጎች በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አመልክተው፤ ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጡ ተግባርም የዓድዋ እሴት በመሆኑ ሁሉም የድርሻዉን እንዲወጣ መጠየቃቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል።