በክልሉ የማካካሻና የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የማካካሻና የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተመላከተ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፤ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚታዩ የተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ ፣ማርፈድና መቅረትን ማረም ይገባል ብለዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ተግባራትን በማጠናከር የማካካሻና የማጠናከሪያ ትምህርት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የማጠናከሪያ ትምህርት ለሁሉም መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይም የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የማዘጋጀቱ ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን በተሳካ መልኩ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወን እንዳለበትም አመላክተዋል።
የትምህርት ለትውልድ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ ሀብት የማሰባሰብ እና መሰል ተግባራቶች ቀጣይነት እንዳላቸው ገልጸው፤ የተማሪዎች የምገባ መርሀግብር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመጋቢት ወር ላይ እንዲጀመር አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው