Fana: At a Speed of Life!

የንብረት ማስመለስ አዋጅን በመጥቀስ ባለሀብቱን አስፈራርተው ገንዘብ በመቀበል የተጠረጠሩት ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ወደ ተግባር ባልገባበትና ምርመራ ባልተጀመረበት ሁኔታ “ንብረታችሁ ሊወረስ ነው” በማለት ባለሀብቱን አስፈራርተው በቼክ ገንዘብ ሲቀበሉ በፀጥታ አካላት ተይዘዋል የተባሉ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ አራት ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሰረተባቸው።

በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበባቸው ተከሳሾች 1ኛ የቦሌ ክፍለከተማ ነዋሪ በግል ስራ የሚተዳደው ተስፋ ሀታኡ፣ 2ኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሞጆ ደረቅ ወደብ ኮንትሮባንድ ሬጅመንት ጥበቃ ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን ካሳ እና 3ኛ ጁዋር አወል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎች ላይ በአንደኛው ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና (ለ) እና የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 28 ንዑስ ቁጥር (3) ድንጋጌን መተላለፍ የሚል እንዲሁም በተደራቢነት በ1ኛ ተከሳሽ ላይ የሙስና አዋጁን አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌን ጠቅሶ ዛሬ ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህም የክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሾቹ በአዲሱ የንብረት ማስመለስ አዋጅ ወደ ስራ ባልገባበት፣ የምርመራ ስራ ባልጀመረበት ሁኔታ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት እንዲመቻቸው 1ኛ ተከሳሽ ለግል ተበዳይ ቢኒያም መሀደር ስልክ በመደወልና መልክት በመጻፍ፣ ሀሰተኛ የፋይናንስ ደህንነት ሰራተኛ የሚል መታወቂያ በማሳየት የባለሀብቱን የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ እና በግል ተበዳይ ሚስት ተመዝገቦ የሚገኘው ቴክ ዳታ ኃላ/የተ/የግል ማህበር የተባለው ድርጅት ክትትል ላይ መሆኑን “በመግለጽ እና የድርጅቱን ዶክመንት ካመጣለት በፋይናንስ ደህንነት እንዳይመረመር እናደርጋለን በማለት ሲደራደር የነበረና የድርጅቱን ዶክመንት እንዲሰጡትና ለጉዳይ ማስፈጸሚያ 10 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ እንዲገባለት ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

የፖሊስ አባል የሆነው 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የግል ተበዳይን በስልክ ደውሎ በማግኘት “ጉዳዩን የያዘውን 1ኛ ተከሳሽን አውቀዋለው የፋይናንስ ደህንነት ሰራተኛ ነው። እኔ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር ተገኛኝቼ ጉዳዩን እጨርስልሀለው” በማለት ጉዳይ ማስፈጸሚያ 10 ሺህ ብር በባንክ ሂሳቡ እንዲላክለት ማድረጉ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ሲደራደሩ ቆይተው በጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም በቦሌ ክ/ከ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው አንዋር ምግብ ቤት ውስጥ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ የባለሀብቱን ጓደኛ በአካል በማግኘት ተከሳሾች የደህንነት አባሎች ነን ብለው በግል ተበዳይ ስም የተፈረመ የአንድ ሚሊየን ብር የአዋሽ ባንክ ቼክ ሲቀበሉ በደህንነትና በፌደራል ፖሊስ የክትትል አባላት እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሌላቸው ስልጣን የመጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ከተከሳሾች መካከል 1ኛ ተከሳሽ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ የደረሰው ሲሆን፤ ቀሪ ተከሳሾችን በየካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ፖሊስ እንዲያቀርባቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.