የተለያዩ ሀገራት ለዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክተው ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባስተላለፈው የመልካም ምኞት መልዕክት÷ የዓድዋ ድል ጽናት፣ አንድነትና ብሄራዊ ኩራትን የሚገልጽ ሁነት ነው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ለኢትዮጵያዊያን ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ስኬትን ተመኝቷል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ ሁለቱ ሀገራት በታሪክ ጀግንነትን፣ አንድነትንና ጽናትን የሚጋሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ከታሪኮቻቸው ባሻገር መጪዎቹ ጊዜያት ብሩህ እንደሚሆኑም እምነቱን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን የጽናትና የአንድነት ምልክት መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ባስተላለፈው መልዕክት÷ ኢትዮጵያዊያንን ለድል ላበቃቸው ጀግንነት፣ አንድነትና ፅናት ክብር እንሰጣለን ብሏል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የኩባ፣ የስሪላንካ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ኤምባሲዎች ለበዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል፡፡