ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ገንብተናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠራዊቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚቃጣ ጥቃትን መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና መገንባቱን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
129ኛ የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመከበር ላይ ይገኛል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ከዓድዋ ድል የምንማረው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዘብ መቆምን ነው ብለዋል።
ከዓድዋ ጀግኖች የድል እሴትን የወረሰው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የትኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና መገንባቱንም ተናግረዋል፡፡
ዓድዋ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ሃይል በማሸነፍ የጥቁር ህዝቦችን ድል አድራጊነት ለዓለም ያስተጋባና የቅኝ ግዛት ዓላማ አራማጆችን ቅስም የሰበረ መሆኑንም አመልክተዋል።
ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም ኢትዮጵያ ጠላቶቿን እያንበረከከች ሉዓላዊነቷን አስከብራ የምትቀጥል ሀገር መሆኗን ጠላትም ወዳጅም መገንዘብ አለበት ብለዋል።
እኛ የዓድዋ ልጆች በዚህ ድል መኩራት ብቻ ሳይሆን የአያቶቻችንን የአይበገሬነትና የድል አድራጊነት መንፈስ በመውረስ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት።
ባለንበት ዘመን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ በመቀበል የሀገርን ጥቅም ለመጉዳት ከጠላት ጋር ለመሰለፍ የሚሞክሩ ባንዳዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን የትኛውም ጠላት አንበርክኳት አያውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ወጀብ በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ ትደክማለች ብለው የሚያስቡ ባንዳዎች ለጠላት ለማጎብደድ ክብራቸውን መሸጥ የለባቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያን የዓድዋ ጀግኖችን እሴትና የጀግንነት መንፈስ የወረሰው ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ይጠብቃታልም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ሠራዊቱ ውስጣዊ አንድነቱ የጠነከረ፣ የሀገር ፍቅር ስሜቱ እጅግ ከፍ ያለ፣ ወታደራዊ ብቃቱ የዳበረ ወኔው የጋለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የምንዘጋጀው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከውጭ የሚቃጡ ጥቃቶችን በብቃት ለመመከት ነው ሲሉም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለዚህም የአየር ሃይል፣ የባህር ሃይል፣ የምድር ሃይልና የሳይበር ሃይላችን ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚመጣ ጠላት የማይበገር ብቻ ሳይሆን ጠላት እንዳይከጅለን የሚያደርግ ቁመና ገንብተዋል ብለዋል።