የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ እንዲገለጥ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ እንዲገለጥ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ እንዲገለጥ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓሉ ለአፍሪካዊያንና መላ ጥቁር ህዝቦች ተስፋንና ድልን ያበሰረና ቅኝ ገዥዎች ሊያጠፉት የነበረን ሰብአዊ ክብር መልሶ ያጎናጸፈ ድል መሆኑን አውስተዋል።
ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጀግንነት ያሳየና የሴቶችን ብርቱ ተሳትፎና የፖለቲካ ጥበብ የገለጠ መሆኑን አስታውሰዋል።
የዓድዋ ታሪካዊ ዳራ ትጉህ የዕውቀት ሃይልና የሀሳብ የበላይነት መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፡ ኢትዮጵያዊያን ከራስ አልፎ ለሌሎች የነበራቸውን ክብር ያሳዩበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ውጤታማ በማድረግ ታላቅነቷን ለማስቀጠል ትውልዱ በጥበብ፣ በዕውቀትና በስራ በመትጋት የዓድዋን ገድል እንዲደግምም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።