የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘብ እንቆማለን – ሌተናል ጄነራል ዘውዱ በላይ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝቡን ሰላም እና የሀገር ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘብ እንቆማለን ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ዘውዱ በላይ አስታወቁ፡፡
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ሐሳብ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
ሌተናል ጄነራል ዘውዱ በላይ በዚህ ወቅት÷ ዓድዋን በመዘከር ኢትዮጵያን አፅንተን ለትውልድ እናሻግራለን ብለዋል።
በዓድዋ ጦርነት ወራሪው የጣሊያን ጦር ሽንፈትን ተከናንቦ የተመለሰበት መሆኑን አውስተው፣ ድሉ የመላ ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
በጅማ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዮናስ ሴፉ፣ ኢትዮጵያዊያን ያኔ የሀገርን ሉዓላዊነት እንዳስከበሩት ሁሉ እኛም ድህነት ላይ በመዝመት እና ሰላምን በማስጠበቅ ልማት በማረጋገጥ ዓድዋን ዛሬ መድገም ይኖርብናል ብለዋል።
በበዓሉ ላይ በሥራቸው የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡና የአገልግሎት ጊዜያቸው የደረሱ የሠራዊቱ አባላት የማዕረግ እድገት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተስፋሁን ከበደ