Fana: At a Speed of Life!

ለማህበረሰቡ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት እየተፈጠረ ነው – ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለማህበረሰቡ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

ሚኒስትሯ እና ሌሎች የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች በጉራጌና ሀድያ ዞኖች በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ዛሬ ተመልክተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንዳሉት÷ በክልሉ በሚገኙ ጤና ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ የሥራ እንቅስቃሴዎችን በመመልከት ያሉ ጠንካራ ጎኖችንና ውስንነቶችን ለመለየት ያለመ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።

በወልቂጤ ከተማ በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ የሚሰጥባቸውን ተቋማት በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በከተማው ግንባታው ያልተጠናቀቀውን ሆስፒታል ከተመለከቱ በኋላ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን በሀድያ ዞን የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታት ከተቋሙ አመራር አባላት ጋር የተሠራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን ማረጋገጣቸውንም አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ ከህክምና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከማህበረሰቡና ከጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በመመለስ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.