ቻይና በኢንዱስትሪዎች ሮቦቶችን በመትከል የሚስተካከላት የለም ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና የኢንዱስትሪዎች ሮቦቶችን በመትከል እና ሥራ ላይ በማሰማራት በዓለም ላይ የቀዳሚነት ሥፍራ እንዳላት ተነገረ።
በፈረንጆቹ 2024 ቻይና ግማሽ ያህል ኢንዱስትሪዎቿ ሮቦቶችን የገጠሙና ወደ ሥራ ያሰማሩ መሆናቸውን የቻይና ህዝብ የፖለቲካ አማካሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ሊዑ ጂኤዪ ተናግረዋል፡፡
ቻይና ዘመናዊውን የኢንዱስትሪ አብዮት በመገንባት እና ጥራት ያላቸው ምርቶች ገበያ ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሳሪያ ማምረቻ፣ የብረታ ብረት እና የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ ቻይና ቀዳሚ እንደሆነች ጠቅሰው፤ በዓለም ላይ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከሚታወቁ 189 የመብራት ፋብሪካዎች መካከል 79 የሚሆኑት በቻይና የሚገኙ መሆናቸውን በአብነት አንስተዋል።
ኢንዱስትሪዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እድገቶች ከፍተኛ መሻሻል ውስጥ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ በዚህም ሮቦቶች ከፍተኛውን ሚና እየተወጡ ነው መባሉን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡